ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ በአማራ ክልል ከ250 ሺህ በላይ ሕጻናት ለአጣዳፊ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12/2016 ዓ.ም ፦ በአማራ ክልል በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ከ250 ሺህ በላይ ሕጻናት ለአጣዳፊ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ ሥርዓተ ምግብ የቅኝት እና ምላሽ ሰጭ ባለሙያ ኃይሌ አያሌው በክልል 43 ወረዳዎች በድርቅ መጎዳታቸውን ጠቅሰው፤ በወረዳዎቹ ከ9 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች በድርቁ ምክንያት የዕለት ምግብ እና ውኃ ፍለጋ አካባቢያቸውን ለቅቀው እንደወጡ ነው ገልጸዋል። 

ባለሙያው ለአሚኮ እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ በክልሉ ባደረገው ሁሉን አቀፍ የምግብ እጥረት ተጠቂዎችን ልየታ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የኾኑ ሕጻናት እና ነፍሰጡር እናቶች ለጤና እና ለሥርዓት ምግብ ይበልጥ ተጋላጭ መኾናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።

“ልየታ ከተሰራላቸው 1 ሚሊዮን 164 ሺህ በላይ ሕጻናት ውስጥ 23 ሺህ የሚኾኑት ከፍተኛ አጣዳፊ የምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ሕክምና እና አልሚ ምግብ ያገኙት 53 በመቶ ብቻ  ናቸው” ብለዋል።

ከ230 ሺህ 300 በላይ የሚኾኑት ሕጻናት ደግሞ መካከለኛ አጣዳፊ የምግብ እጥረት እንዳለባቸው የገለፁት ኃይሌ አያሌው ከእነዚህ ውስጥም ድጋፍ ያገኙት 15 በመቶ ብቻ መሆናቸውን አመላክተዋል። 130 ሺህ 977 መካከለኛ የምግብ እጥረት ካለባቸው እናቶች ውስጥ 11 በመቶ የአልሚ ምግም ድጋፍ አግኝተዋል ብለዋል።

በአቅርቦት ችግር እና የቀረበውንም በክልሉ በተከሰተው “የፀጥታ እና ሌሎች ችግሮች” ምክንያት ተደራሽ ማድረግ ባለመቻሉ ሕጻናት እና እናቶች ለከፍተኛ የምግብ ችግር መጋለጣቸው ነው ባለሙያው  የገለጹት።

በድርቁ ምክንያት ከተከሰተው ሥርዓተ ምግብ ባለፈ እንደ ኩፍኝ፣ አባሰንጋ፣ ትክትክ፣ ኮሌራ የመሳሰሉ በሽታዎች ሌላኛው ችግር እንደነበር አንስተዋል።  አሁንም ከችግሩ ያልተላቀቁ ወረዳዎች መኖራቸውን አክለው ገልጸዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ችግሩን መንግሥት ከሚያደርገው አቅርቦት ባለፈ በክልሉ የሚገኙ ተቋማት፣ ረጅ ድርጅቶች እና ማኅበረሰቡ  ድጋፍ  እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል ሲል አሚቾ ዘግቧል።

ዪኒሴፍ ትላንት ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ በኢትዮጵያ 10.8 ሚሊዮን ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 20 ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ደጋፍ ያስፈልጋቸዋል ሲል አስታወቋል።  

በ2023 የድርቅ፣ ግጭት፣ ጎርፍ እና በሽታዎች ተጽዕኖ 31.4 ሚሊዮን ሰዎች ድጋፍ እንዲሹ መደረጉ እና  7.6 ሚሊዮን ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲሆኑ አድርጓል ብሏል።

ይህ በእንዲህ እያለ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ለ6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ 500 ሚሊዮን ዶላር እንድሚያስፈልገው አስታውቋል። 

500 ሚሊዮን ዶላር የሚያስፈልገው በትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ሶማሌ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ድሬዳዋ፣ ጋምቤላና ሐረሬ ለሚገኙ ተረጂዎች ከጥር እስከ መጋቢት ዕርዳታ ለማቅረብ መሆኑን ቢሮው ገልጧል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button