ዜናህግ እና ፍትህ

ዜና: በኮንሶ፣ በብሔረሰቦች መካከል ግጭት በማስነሳት ነዋሪዎች እንዲፈናቀሉና የሰዎች ህይወት እንዲጠፋ ያደረጉ ተከሳሾች በ19 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28/2016 ዓ.ም፡- በኮንሶ፣ኩሱሜ እና ደራሼ ብሔረሰቦች መካከል ግጭት በማስነሳት ከ11 ሺህ በላይ ነዋሪዎች እንዲፈናቀሉ እንዲሁም የሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ ያደረጉ ተከሳሾች በ19 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጡ።

በጽኑ እስራት እንዲቀጡ የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አርባ ምንጭና አካባቢው ተዘዋዋሪ ወንጀል ችሎት ነው።

የፍትሕ ሚኒስቴር የፌዴራል የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ህዳር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በሰባት ግለሰቦች ላይ ተደራራቢ ክስ አቅርቦ ነበር።

ክሱ ቀርቦባቸው የነበሩ 1ኛ አበበ አያኖ፣ 2ኛ ከበደ አርሳይዶ፣ 3ኛ ግርማ ባንሶ፣ 4ኛ በቀለ ባልቻ፣ 5ኛ አባተ ዱቡ፣ 6ኛ ታምሩ ዳጋቴ እና 7ኛ ወገኔ ጋሃኖ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው።

ተከሳሾቹ ለጊዜው እጃቸው ካልተያዙ ግብረ-አበሮቻቸው ጋር በመሆን ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ጥያቄ ሲቀርብበት የነበረውን የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ ጋር በተገናኘ መነሻ በማድረግ በኮንሶ፣ኩሱሜና ደራሼ ብሔረሰብ መካከል ለግጭት በማነሳሳትና በመቀስቀስ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ መቆየታቸው በክስ ዝርዝሩ ተጠቅሷል።

በተለይም በየካቲት 16 ቀን 2014 ዓ.ም ከረፋዱ 4:00 አካባቢ በደራሼ ልዩ ወረዳ፣ጋቶ ቀበሌ፣በኮንዞ ዞን ሰገንና ካራት ዙሪያ ወረዳ፣ገርጩና አይሎታ ደከቱ ቀበሌዎች መካከል የሚገኝ ቱርባ ኮልባ አልባጮ የተባለ ለም የእርሻ ማሳዎች መነሻ አድርገው ባስነሱት የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ በመሳተፍ መንደር ሁለት ወደ ሚባል አካባቢና ወደ ሌሎች የገጠር አካባቢዎች የእርስ በርስ ግጭቱን ማስፋፋታቸውን ዐቃቤ ህግ በክስ ዝርዝሩ ላይ አስፍሯል።

ባስነሱት ግጭት በመሳተፍ ከሚያዚያ 17 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ገጀራ፣ቆንጨራ እና የተለያዩ የጦር መመሪያዎችን በመያዝ የጋቶ ቀበሌና የሌሎች ነዋሪ የነበሩ 10 ሰዎች ላይ ጥቃት በመክፈትና ሕይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጋቸውም ተጠቅሷል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በዚህም 864 ሚሊየን 142 ሺህ 575 ብር ከ 57 ሳንቲም የሚገመቱ የመንግስት፣የህዝብና የግለሰብ ንብረቶች ላይ ጉዳት በማድረስና 11 ሺህ 624 ሰዎችን ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጋቸው ተጠቅሶ በዝርዝር ክሱ ላይ ተመላክቷል።

ተከሳሾቹ ክሱ ከደረሳቸውና በችሎት በንባብ ከተሰማ በኋላ የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምንም በማለት የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ከ10 በላይ የሰው ምስክሮች በችሎት አቅርቦ አሰምቷል፡፡

ተዘዋዋሪ ችሎቱ በተከሳሾች ላይ የተሰሙ የምስክሮችን ቃል እና ተያያዥ የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ በክሱ ዝርዝር ላይ የተጠቀሰው የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን ማረጋገጡን ጠቅሶ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

በተሰጠው ብይን መሰረት ተከሳሾቹ የመከላከያ ምስክሮችን ያቀረቡ ቢሆንም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን ግን በተገቢው መከላከል አለመቻላቸው ተገልጾ አምስት ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

ከእነዚህ ተከሳሾች ጋር አብረው ተካተው የነበሩ 6ኛ እና 7ኛ ተከሳሾችን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ የቀረበባቸውን ክስ በተገቢው የተከላከሉ መሆኑን ገልጾ በነጻ አሰናብቷቸዋል።

ከዚህም በኋላ ተዘዋዋሪ ችሎቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየትን በመያዝ ጥፋተኛ የተባሉትን ከ1ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ19 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን ከፋና ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button