ዜናጤና

ዜና፡ የፆታዊ ጥቃት ህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከል በቅዱስ #ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተመርቆ ተከፈተ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12/2016 ዓ.ም፡- የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የፆታዊ ጥቃት ህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከል በሆስፒታሉ ግቢ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑን አስታወቀ።

ማዕከሉ በዓለም ላይ ብሎም በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ለመከላከል እና ጥቃት ለደረሰባቸው ተጎጂዎች የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ የተከፈ መሆኑን ከሆስፒታሉ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ማዕከሉ በኬዝ ማናጀር ደረጃ የተከፈተ እና የተለያዩ ባለሙያዎችን በማካተት በቀጣይ የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጠት እንዲችል ሆኖ የተደራጀ በመሆኑ ከጥቃቱ አልፎ የህክምና አገልግሎት በማጣት በተጠቂዎች ላይ የሚደርሰውን እንግልት በማስቆም ረገድ ወሳኝ ሚና የሚኖረው ይሆናል ሲሉ የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አብርሀም እሸቱ መናገራቸውንም መረጃው አስታውቋል።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ዮሐንስ ኃይለሚካኤል በበኩላቸው ማዕከሉ የተገዶ መደፈር አደጋ ደርሶባቸው ለሚመጡ ተጎጂዎች ያልታሰበ እርግዝናና ሌሎች የአባላዘር ህመሞች እንዳይከሰቱባቸው የመከላከል ህክምና አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች፣ ህጻናት እና ወንዶች ልጆች የማኅበራዊ ፣ ስነ ልቦናዊ እንዲሁም የህግ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን መግለጻቸውንም ጠቁሟል።

ሆስፒታሉ በሚገኝበት የጉለሌ ክፍለ ከተማ የፆታዊ ጥቃት ቁጥር ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ ተጠቂዎች የተቀናጀ አገልግሎት በአንድ ቦታ ማግኘት እንዲችሉ፤ ጥቃት አድራሾችም ሳይውል ሳያድር የሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ፓሊስና አቃቤ ህግ ተመድቦ አገልግሎት እንደሚሰጥ እንዲሁም ተጠቂዎች ሚስጢራዊነቱ በተጠበቀ ሁኔታ አገልግሎትና ፍትህ በማዕከሉ እንዲሚያገኙ የተናገሩት ደግሞ የሆስፒታሉ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሲ/ር ተወዳጅ መርሻ ናቸው ብሏል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button